![]() | ![]() |
ጳጉሜን 5 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዲ/ን ዘላለም ቻላቸው
"የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል" /1ኛ.ጴጥ.4.3/
![]()
የዘመን አቆጣጠርን መጀመር አስፈላጊ ያደረጉ ሁለት ዋና ዋናምክንያቶች ነበሩ፡-
1. አዳም በበደሉ ምክንያት ከገነት ተባሮ ወደዚች ምድር ሲመጣ በመጸሐፈ ቀሌምጦስ እንደተጠቀሰው እግዚአብሔር «ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ» ብሎት ነበር፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ አንድ ቀን አንድ ሺሕ ዓመት መሆኑንና ይህ አምስት ቀንተኩል የተባለው ጊዜ 5500 ዓመት መሆኑን አዳምም ፣ ቀደምት አበውም ያውቁ ነበር እግዚአብሔር ዕፀ በለስን እንዳይበላ አዳምን ሲያዘው «ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞትለህ» ብሎት ነበር /ዘፍ.2.17፡፡ ይሁን እንጂ አዳም የሞተው በሰው አቆጣጠር 970 ዓመት ኖሮ ነው፡፡ይህ እግዚአብሔር ቀን ብሎ የገለጸው ምን ያህል እንደሆነ ለአዳም የሚያሳውቅ ነበር፡፡
ክቡር ዳዊትም "ሺሕ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትናንት ቀን እንደ ሌሊትም ሰዓት ነውና" /መዝ.89.4/ በማለት መናገሩ ደግሞ ቀደምት አበው ስሌቱን እንደሚያውቁት የሚጠቁም ነው፡፡እንግዲህ አበውና ነቢያት ይህንን በተስፋ ሲጠብቁት የነበረውን የእግዚአብሔርን የማዳን ቀን የሚቆጥሩት የዘመን አቆጣጠር አስፈለጋቸው፡፡
2. የሰው ልጆች ወደ ምድረ ፋይድ ከወረዱ በኃላ "በሕይወትህ ዘመን ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ.. ወደ መጣህባት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ » /ዘፍ.2 .16-17/ በሚለው አምላካዊ ቃል መሠረት የሚበሉትን ለማግኘት የግብርና እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ጀምረው ነበር፡፡በዚህ ጊዜ አየሩ የሚሞቅበትንና የሚቀዘቅዝበትን፣ ዝናም የሚኖርበትንና የማይኖርበትን፣ ቀኑ የሚረዝምበትንና የሚያጥርበትን ጊዜ ለማወቅና ሥራን ከዚህ አንጻር ለማቀድና ለመተግበር የዘመን መቁጠሪያና የጊዜ መስፈሪያ አስፈልጓቸዋል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች የሰው ልጆች የተለያዩ መስፊሪያዎችን /መለኪያዎችን/ በመጠቀም ጊዜን / ዘመንን ሰፍረዋል፡፡ በሁሉም ቦታ የነበሩትና ዐበይት የሚባሉት የዘመን መስፈሪያዎች እግዚአብሔር «ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ፣ ለዕለታት፣ ለዘመናትና ለዓመታት ምልክት ይሆኑ ዘንድ» / ዘፍ.1. 14- 15/ የፈጠራቸውን የፀሐይንና የጨረቃን እንቅስቃሴ መሠረትያደረጉት መስፈሪያዎች ናቸው፡፡ እነዚህም፡- ሀ. ዕለት- አንድ ዕለት አንድ ቀንን /የብርሃን ክፍለ ጊዜን / እና አንድ ሌሊትን /የጨለማ ክፍለ ጊዜን/ ያካተተ ፀሐይ አንድ ጊዜ ከወጣች በኋላ ተመልሳ እስክትወጣ ድረስ ያለውን ጊዜ የያዘ ነው፡፡ በአሁኑ ዕውቀታችን አንድ ዕለት ምድር በራሷ ዛቢያ አንድ ጊዜ የምትሸከረከርበት ጊዜ ነው፡፡ ለ. ውርኅ- ወርኅ ማለት በግእዝ ጨረቃ ማለት ነው፡፡ አንድ ወርኅ የሚባለው ጊዜ ሙሉ ጨረቃ ከወጣች በኋላ ድጋሚ እስከምትወጣ ድረስ ያለው ጊዜ ነው፡፡ በአሁኑ ዕውቀታችን / በጥንቱም ጨምሮ/ ይህ ጨረቃ መሬትን አንድ ጊዜ ዙራ ለመጨረስ የሚፈጅባት ጊዜ ነው፡፡ አንድ ወር ሃያ ዘጠኝ ተኩል ዕለታትን ይፈጃል፡፡ ሐ. ዓመት- አንድ ዓመት ማለት መሬት አንድ ጊዜ በፀሐይ ዙሪያ ለመዞር የሚፈጅባት ጊዜ ነው፡፡ ይህም 365 ከ1/4 / ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ቀን ከሩብ/ ዕለታት ይፈጃል፡፡ይህ ከመታወቁ በፊትም ግን የዓመት ጽንሰ ሓሳብ ነበር፡፡
ሰዎች ርዝመታቸው እኩል የሆኑ ሁለት ሻማዎችን ሠሩና ልክ ፀሐይ ስትወጣ /ቀኑ ሲያልቅና ሌሊቱ ሲጀምር/ አንዱን ሻማ አበሩት፡፡ ልክ ፀሐይ ስትወጣ እሱን አጠፋናሌላውን / ሁለተኛውን/ ሻማ አበሩት፤ ጧት ፀሐይ እንደገና ስትወጣ / ሌሊቱ አልቆ ሌላ ቀን ሲጀምር/ ሻማውን አጠፉት፡፡ አሁን እንግዲህ ከየሻማዎቹ /ከሁለቱ ሻማዎች/ ምን ያህል እንደተቃጠለላቸው ሲያስተያዩት ከሁለቱ ሻማዎች የተቃጠለው እኩል አለመሆኑን ተመለከቱ በዚህም የቀኑና የሌሊቱ ርዝማኔ እኩል አለመሆኑን ተረዱ፡፡ ቀደም ብለውም የቀኑና የሌሊቱ ርዝማኔ በተለያዩ ወቅቶች የተለያየ መሆኑን ልብ ብለው ነበርና ይህንን ሙከራቸውን ሲቀጥሉ በቀኑና በሌሊቱ ርዘማኔ /በሚቃጠለው የሻማዎቹ መጠን/ መካከል ያለው ልዩነት ከወቅት ወቅት የተለያየ እንደሆነ ተመለከቱ፡፡ ይህን ሙከራቸውን ሲቀጥሉ ግን በየ182 /ተኩል/ ዕለቱ ቀኑና ሌሊቱ እኩል የሚሆኑባቸው ሁለት ዕለታት በዓመት ውስጥ እንዳሉ ተገነዘቡ፡፡ እነዚህ ዕለታት አንዱ የሙቀት ወራት ከመጀመሩ በፊት የሌላው ደግሞ የቅዝቃዜው ወራት ከመጀመሩ በፊት የሚመጡ ናቸው፡፡ ስለዚህ የቀኑና የሌሊቱ ርዝመት አንድ ጊዜ እኩል ሁኖ ደግሞበዚያው ወቅት እኩል እስከሚሆን ድረስ ያለውን ጊዜ ማለትም /182 ተኩል +182=365/ ዕለት አንድ ዓመት አሉት፡፡ አሁን ባለን ግንዛቤ ምድር በራሷ ዛቢያ እንደተሽከረከረች በፀሐይ ዙሪያ ትዞራለች፡፡ ምድር በፀሐይ ዙሪያ የምትዞረው ወደ ጎን 23 ተኩል ዲግሪ ያህልአጋድላ ነው፡፡ ይህ የቀንና የሌሊት ርዝመት መለያየትም የሚከሰተው በዚህ ማጋደል ምክንያት ነው፡፡
እንግዲህ በአጠቃላይ ዋናዎቹ የጊዜ / የዘመን/ መስፊሪያዎች ዕለት፣ ወር እና ዓመት ናቸው፡፡ ሦስትቱም ተመላላሽ ክስተቶችን / ለምሳሌ የፀሐይን መውጣት/ መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡ እነዚሀ ተመላላሽ ክስተቶች አንድ ጊዜ ከተከሰቱ በኋላ ደግመው እስኪከሰቱ የሚፈጁት ዘመንnወይም ጊዜ ዓውድ ይባላል፡፡ ዓውድ ማለት ዙሪያ፣ ክብ፣ እንደ ቀለበት ዙሮ የሚገጥም ማለት ነው፡፡ ስለዚህዓውድ ማለት ክስተቶቹ አንድ ጊዜ ከተከሰቱ በኋላ ደግመው እስኪመጡ ድረስ ያለው ጊዜ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ከላይ ያየናቸው ሦስት መስፈሪያዎች/ ዕለት፣ ወርኀ፣ ዓመት/ ዓዕዋዳት / ዓውዶች/ የሚወጡበት ጊዜ ዓውደ ዕለት፣ ዓውደ ወርኀ፣ ዓውደ ዓመት ይባላሉ፡፡
መጀመሪያ ላይ ሰዎች እነዚህን ሦስቱን መስፈሪያዎች /ዓዕዋዳት/ /በተለይም ቀንና እና ወርን/ለየብቻቸው ይጠቀሙባቸው ነበር፡፡ ከዚህን ያህል ቀን፣ከዚህን ያህል ወር በኋላ /በፊት/ እያሉ ጊዜን ይለኩ ነበር፡፡ እነዚህ ሦስቱን በቅንብር/በቅንጅት/ ለመጠቀም ሲፈለግ ግን የዘመን አቆጣጠር ስሌት ያስፈልጋል፡፡ምክንያቱም አንድ ወር 29 ከግማሽ ቀን ነው፡፡ እንዲሁ እንዳለ ለመቁጠር ቢፈለግ የመጀመሪያው ወር ጠዋት ላይ ቢጀመር ሁለተኛው ወር ምሽት ላይ ይጀምራል፣ ሦስተኛው ደግሞ ድጋሚ ጠዋት ላይ ይጀምራል፤ ይህን ለመቅረፍ ወሩን ሙሉ ሰላሳ ቀን ቢያደርጉት ከትክክለኛው ወር /የጨረቃ ዐውድ/ ግማሽ ቀን ይተርፋል፤ 29 ቀን ብቻ ቢያደርጉት ደግሞ ግማሸ ቀን ይጎድላል፡፡ አንድ ዓመት 365 ከሩብ ዕለታት አሉት፡፡ ዓመትን በወራት ለመቁጠር ቢፈለግ፤ዓመቱን 12 ወር ቢያደርጉት የዓመቱ /የዕለታት ቁጥር /29.5X12=354/ ብቻ ይሆናል፡፡ይህም ከትክክለኛው ዓመት /365-354=11/ ዕለታት ያህል ያንሳል፡፡13 ወር ቢያደርጉት ዓመቱ /365X13=385.5/ ቀናት ይሆናል ይህም ከትክክለኛው ዓመት /383.5-365=19/ ቀናት ያህል ይበልጣል፡፡ ስለዚህ እነዚህን መስፈሪያዎች በቅንጅት ለመጠቀምይህንን አለመጣጣም የሚፈታ ቀመር /የዘመን አቆጣጠር ሥርዓት/ ያስፈልጋል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ የዘመን አቆጣጠሮች ተዘጋጅተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የአይሁድን፣የሮማውያንን እና የሀገራችንን አቆጣጠሮች በአጭሩ እንመለከታለን፡፡ የአይሁድ ዘመን አቆጣጠር የአይሁድ ዘመን አቆጣጠር እያንዳንዳቸው 29 እና 30 ዕለታት ያሏቸው 12 ወራት አሏቸው፤ |