ሥራህን ሥራ
በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ
ጌታ ለእያንዳንዱ ሰው ሥራ ሰጥቶታል፤ ያንን መሥራት የእሱ ፈንታ ነው። ቢቻለው እሱን ማገድ የዲያብሎስ ሥራ ነው። በርግጥ ሥራውን እግዚአብሔር እንደሰጠህ ያህል ሰይጣን ሊያግድህ ይጥራል። በበለጠ ደስ የሚያሰኝ ሌላ ነገር ሊያቀርብልህ ይጥራል፤በዓለማዊ ተስፋዎች ያባብልሃል። የሐሜት ጎርፍ ያስወርድብሃል። ደራሲያን እንዲጠይቁህ፣እጅግ ስመጥር ሰዎችም በክፉ እንዲናገሩብህ ይጠቀምባቸዋል።
ጲላጦስ፤ ሔሮድስ፤ ሐናንያ፤ ቀያፋ ሁሉም በአንተ ላይ ያድማሉ። ይሁዳም በአጠገብህ ቆሞ በሰላሳ ብር ሊሸጥህ ይከጅላል። ይሄ ሁሉ የደረሰብህ ሰይጣን በዚህ ከሥራህ ሊስብህና እግዚአብሔርን ከመታዘዝ ሊያሰናክልህ መሆኑን ልትገነዝብ አትችልምን?
ሥራህን ሥራ፦ ዓላማህ እንደ ኮከብ የጸና ይሁን:: ዓለም እንደፈለገው ይነታረክ ይጨቃጨቅ፡ተወው ፡ አንበሳው ሲያገሳ ፍንክች አትበል የሰይጣንን ውሻዎችን ለመውገር አትቁም፡፡ ጥንቸሎችን በማባረርም ጊዜህን አታጥፋ።
ሥራህን ሥራ፦ ዋሾች ይዋሹ፣ ጠበኞች ይጣሉ፣ ማኅበሮችም ይወስኑ፣ ደራሲዎችም ይድረሱ፤ ሰይጣንም የፈለገውን ያድርግ። አንተ ግን እግዚአብሔር የሰጠህን ሥራ ከመፈፀም ምንም ነገር እንዳያግድህ ተጠንቀቅ።
ሥራህን ሥራ፦ ገንዘብ እንድታተርፍ አልተላክህም፣ እንድትበለጽግም አልታዘዝክም፣ ለክብርህ ተከላከል ተብሎ አልተነገረህም፤ ሰይጣንና አገልጋዮቹ የሚነዙትን የሐሰት ወሬ እንድታስተባብል አልተጠየቅህም እነኚህን ሁሉ ነገሮች ብታደርግ ሌላ ሥራ ልትሰራ አትችልም፤ ይህም ብቻ ሳይሆን ለራስህ እንጂ ለጌታ አልሰራህም።
ሥራህን ሥራ፦ ዓላማህ እንደ ዐለት የፀና ይሁን፣ ጥቃት ይደርስብህ፣ ትበደል፣ትሰደብ፣ ትታማ፤ ትቆስልና ትናቅ ይሆናል። አንተ ግን በፀና ውሳኔ የማያወላውል ቅናት በመጨረሻ ላይ ፀንተህ “የሰጠኸኝን ሥራ ፈፀምኩ ሃይማኖትንም ጠበቅሁ” ለማለት እስክትችል ድረስ የሕይወትህን ዓላማና የተፈጠርክበትን ግብ ተከተል።