አለን ባሕራኖች ምሥክር የሥምህ፣
ሚካኤል አያልቅም ተነግሮ ተዓምርህ፡፡
‹‹ሚካኤል ሆይ መሬትና ውሃ ያልተቀላቀለበት ከነፋስና ከእሳት ብቻ ለተፈጠረው መልአካዊ ገጽታህ ሰላም እልሃለሁ›› (መልክአ ሚካኤል (ለገጽከ))
ይህ ግሩም መልአክ ሣጥናኤልን ተዋግቶ የጣለው ፣ ዳንኤልን ከአናብስት ፣ ጴጥሮስንም ከእሥር ቤት የታደገው ነው፡፡ የአፎምያ ጋሻ ለሚጠሩትም ሁሉ መከታ፣ እስራኤልን ከምድረ ግብጽ እስከ ከነዓን የመራቸውም እርሱ ነው ፤ ቀኑን በደመና ሌቱን በብርሃን ዓምድ፡፡ ለማኑዔም ብሥራትን ያሰማው ፤ ሚስቱም ትወልድ ዘንድ በዘር ፍሬ የባረካት እርሱ ነው፡፡ መላእክትን ሁሉ ለልዑል ያሰግዳቸዋል እርሱም ይሰግዳል ፡፡ ሚካኤል የስሙ ትርጓሜ ‹‹መኑ ከመ እግዚአብሔር››(ማን እንደ እግዚአብሔር)ነው፣ አንድም ‹‹መልአከ ምክሩ ለእግዚአብሔር››(የእግዚአብሔር አማካሪው) ይባላል፡፡ መላእክት ነገዳቸው መቶ ሲሆን ሊቃነ በናብርቱ ደግሞ ሰባት ናቸው የሰባቱ ደግሞ ሊቃቸው ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡ ልብሱ መብረቅ ፣ ገጹ እሳት ፣ ድምጹም ነጎድጓድ ነው ፡፡ ግብጽ የኃጢአት(የሲዖል) ፣ ከነዓን ደግሞ የጽድቅ ምሣሌ ናቸው እርሱም እስራኤል ዘሥጋን ከግብጽ ወደ ከነዓን እንደመራቸው ዛሬም በምልጃው ለሚታመኑ በኪዳኑ ለጸኑ ሁሉ ዘወትር ፈጥኖ ደራሽ እና ታዳጊ ነው፡፡ ለዚህ ግሩም መልአክ ለክብሩ ሥግደት እና ምሥጋና ይገባዋል ፡፡ በተሰጠው ኪዳነ ምልጃም ፍጥረቱን ይታደግ ዘንድ በመጨረሻው ዘመን ስለ ሕዝብ ሁሉ ይቆማል ት.ዳን 12፡1 ፡፡ ከመልአኩ ምልጃና ረድኤት ፣ ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን(ይቆየን)፡፡