ምድርም በክርስቶስ ደም ታጥባ የፋሲካን በዓል ታከብራለች፡፡ /ድጓ ዘፋሲካ/ | ![]() | ![]() |
ሚያዚያ 02ቀን 2007ዓ.ም
መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ
![]() ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ካስተማረ በኋላ አስቀድሞ ለአዳምና ለሔዋን ሞታቸውን ሊሞት፤ዕዳቸውን ደመስሶ ነጻ ሊያደርጋቸው በገባው ቃል ኪዳን መሠረት መከራን ተቀበለ፤ በአይሁድ ሸንጎ ፊት ቆመ፣ ምራቅ ተተፋበት፣ ተገረፈ፣ በገመድ ታስሮ ተጎተተ፣ በመስቀል ተሰቅሎ መለኮት በሥጋ ሞተ፣ የአዳምና የሔዋንን ዕዳ በደል ደመሰሰ፡፡ ሞትን ድል አድርጎ ነጻ አወጣቸው፡፡ ማቴ. 27-28 ይህንን የቤዛነት፣ የነጻነትና የድል በዓል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች በየዓመቱ ጌታ የጾመውን ጾም ከጾሙ በኋላ መከራውን ሥቃዩን ከሆሳዕና በዓል ጀምሮ በማሰብ፤ በጥንተ ጠላታችን አማካኝነት አይሁድ ክብርህን ዝቅ ቢያደርጉ፣ ቢያዋርዱህ፣ ቢገርፉህ፣ ቢሰቅሉህና ቢገድለህ እኛ ግን ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፡፡ አማኑኤል አምላኪዬ ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ ወአወስከ ለዓለመ ዓለም፣ ኃይሌ መከታዬ ረዳቴ የሆንኸው ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ለአንተ ክብርና ምስጋና ይገባል እያልን እናመሰግንለን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በፊል. 3፡10 ላይ እንደጠቀሰው እርሱንና የትንሳኤውን ኃይል እንዳውቅ በመከራውም እንድካፈል ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ፡፡እንዳለው የእምነቱ ተከታዮች እንደ አቅማቸው እያዘኑ፣ እያለቀሱ፣ ከምግብ እየተከለከሉ፣ የአምላካቸውን መከራ ያስባሉ፡፡ ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቷልየሚለውን የምሥራች ከቤተ ክርስቲያናቸው ለመስማት በናፍቆት ይጠብቃሉ፡፡ ትንሳኤውም ይበሰርላቸዋል፡፡ ጌታ በእውነት ተነሥቷል እያሉ ይመሰክራሉ፡፡ ትንሳኤው የድኅነት ብስራት በመሆኑ ለሃምሳ ቀናት ያህል ብስራቱ በቤተ ክርስቲያን በቅዳሴው፣ በማኅሌቱ፣ በወንጌሉ ወዘተ. ይዘከራል በማንኛውም ቦታ ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ እየተባለ ሞት መደምሰሱን ነጻነት መታወጁን በሰላምታ ይበሰራል፡፡ በየዘመኑ የተነሡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ስለ ክርስቶስ ትንሳኤ ከዚህ ቀጥሎ የተገለጠውን ትምህርትና ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቶ ሲኦልን ረግጦ፣ በሞቱ ሞትን አጠፋው፤ እንደ ሞተ እንዲሁ ተነሣ፣ ሙታንንም አስነሣ፤ እንደተነሣም እንዲሁ ሕያው ነው፤ አዳኝ ነው፡፡ በዚህ ዓለም እንደዘበቱበት፣ እንደሰደቡት፤ እንዲሁ በሰማይ ያሉ ሁሉ ያከብሩታል፤ ያመሰግኑታል፡፡ ለሥጋ በሚስማማ ሕማም ተሰቀለ፤ በእግዚአብሔርነቱ ኃይል ተነሣ፣ ይኸውም መለኮቱ ነው፡፡ ወደ ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን ማረከ፡፡ /ቅዱስ ሄሬኔዎስ ሃይ. አበ. 7፥28-31/ እንዲል፡፡ሰው ሆኖም ሰውን ፈጽሞ ያድን ዘንድ ታመመ፣ ሞተ፣ ተቀበረ፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡/ዘሠለስቱ ምዕት 19፥24/ እያሉ የክርስቶስን የማዳን ሥራ አስተምረዋል፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ ሥጋ ከመለኮቱ ሳይለይ በመቃብር አደረ፤ ነፍሱም ከመለኮት ሳትለይ በገሃነም ተግዘው ለነበሩ ነፍሳት ደኅነትን ታበስር ዘንድ፤ ነጻም ታደርጋቸው ዘንድ ወደ ሲኦል ወረደች፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንደተናገረው ቃል ዐፅም ሥጋ ወደ መሆን ፈጽሞ እንደተለወጠ የሚናገሩ የመናፍቃንን የአእምሮአቸውን ጉድለት ፈጽመን በዚህ ዐወቅን፤ ይህስ እውነት ከሆነ ሥጋ በመቃብር ባልተቀበረም ነበር፤ በሲኦል ላሉ ነፍሳት ነጻነትን ያበስር ዘንድ ወደ ሲኦል በወረደ ነበር እንጂ፡፡ ነገር ግን ከነፍስና ከሥጋ ጋር የተዋሐደ ቃል ነው፤ እርሱ የሥጋ ሕይወት በምትሆን በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ለነፍሳት ነጻነትን ሰበከ፡፡ ሥጋ ግን በበፍታ እየገነዙት በጎልጎታ በዮሴፍ በኒቆዲሞስ ዘንድ ነበረ፤ ቅዱስ ወንጌል እንደተናገረ፡፡ አባቶቻችን ሥጋ በባሕርዩ ቃል አይደለም፤ ቃል የነሣው ሥጋ ነው እንጂ ብለው አስተማሩን፤ ይህንን ሥጋም ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ቶማስ ዳሠሠው፤ በሥጋው ሲቸነከር ቃል ታግሦ የተቀበለውን የችንካሩን እትራትም በእርሱ አየ፡፡ /ቅዱስ አትናቴዎስ ሃይ. አበ. 25፥40፣30፥31-36/ ቅዱስ ባስልዮስም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ሲያስተምር አሁን እግዚአብሔር ሞተ ሲል ብትሰማ አትፍራ፤ የማይሞተውን ሞተ ሊሉ አይገባም ከሚሉ ዕውቀት ከሌላቸው፤ ሕማሙን፣ ሞቱን ከሚክዱ መናፍቃን የተነሣ አትደንግጥ፡፡ እኛ ግን በመለኮቱ ሞት እንደሌለበት፤ በሥጋ ቢሞትም በመለኮቱ ሥልጣን እንደ ተነሣ እናውቃለን፤ ሞት የሌለበት ባይሆንስ ኖሮ በሥጋ በሞተ ጊዜ ሥጋውን ባላስነሣም ነበር፤ ሥጋው እስከ ዓለም ፍጻሜ በመቃብር በኖረ ነበር እንጂ፡፡ /ቅዱስ ባስልዮስ ሃይ. አበ. 34፥17-18/ ብሏል፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ከመስቀሉ ወደ ሲኦል በመውረዱ አዳነን፤ በአባታቸው በአዳም በደል በሲኦል ተግዘው የነበሩ ጻድቃንን ፈታ፤ ከሙታን ተለይቶ አስቀድሞ በተነሣ በእውነተኛ ትንሣኤውም አስነሣን፤ የንስሐንም በር ከፈተልን፡፡ አባታችን በአዳም በደል የተዘጋ የገነት ደጅን የከፈተልን፤ ዕፀ ሕይወትን የሚጠብቅ ኪሩብንም ያስወገደው፤ የእሳት ጦርን ከእጁ ያራቀ፤ ወደ ዕፀ ሕይወት ያደረሰን እርሱ ነው፤ ፍሬውንም /ሥጋውን፤ ደሙን/ ተቀበልን፡፡ አባታችን አዳም ሊደርስበት ወደ አልተቻለው፤ በራሱ ስሕተት ተከልክሎበት ወደነበረው መዓርግ ደረስን፤ ክፉውንና በጎውን ከሚያስታውቅ፤ ወደ ጥፋት ከሚወስድ፤ በአዳምና በልጆቹም ላይ ኃጢአት ከመጣበት ከዕፀ በለስ ፊታችንን መለስን፡፡ /ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ 36፥30፣ 36፥38-39/ በማለት አስተምሯል፡፡ ቅዱስ አቡሊዲስ በሃይማኖት አበው እንደተዘገበው ሲያስተምር የሕይወታችን መገኛ የሚሆን የክርስቶስ ሞት የእኛን ሞት ወደ ትንሣኤ እንደለወጠ እናምናለን፤ ክርስቶስም ሞትን አጥፍቶ የማታልፍ ትንሣኤን ገለጠ፤ እንደተጻፈ፡፡ ከሰው ወገን ማንም ማን ሞትን ያጠፋ ዘንድ፣ ትንሣኤንም ይገልጣት ዘንድ አይችልም፤ ዳዊት በሕያውነት የሚኖር፤ ሞትንም የማያያት ሰው ማነው? ነፍሱን ከሲኦል፤ ሥጋውን ከመቃብር የሚያድን ማን ነው? ብሎ እንደተናገረ፡፡/ቅዱስ አቡሊዲስ ሃይ. አበ. 42፥6-7/ ሲል ቅዱስ ኤራቅሊስም በመለኮትህ ሕማም ሞት የሌለብህ አንተ ነህ፤ በሥጋ መከራ የተቀበልክ አንተ ነህ፤ ከአብ ጋር አንድ እንደ መሆንህ ሞት የሌለብህ አንተ ነህ፤ ከእኛም ጋር አንድ እንደመሆንህ በፈቃድህ የሞትክ አንተ ነህ፡፡ በመቃብር ያደርህ አንተ ነህ፤ በኪሩቤል ላይ ያለህ አንተ ነህ፤ ከሙታን ጋር በመቃብር የነበርህ አንተ ነህ፤ በአንተ ሕማምና ሞትም ድኅነት ተሰጠ፤ ከሙታን ጋር የተቆጠርህ አንተ ነህ፤ ለሙታንም ትንሣኤን የምትሰጥ አንተ ነህ፡፡ ሦስት መዓልት፤ ሦስት ሌሊት በመቃብር ያደርህ አንተ ነህ፤ በዘመኑ ሁሉ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የምትኖር አንተ ነህ፤ በመለኮት ሕማም ሳይኖርብህ በሥጋ የታመምክ አካላዊ እግዚአብሔር ቃል አንተ ነህ፡፡ /ቅዱስ ኤራቅሊስ 48፥12-13/ ቅዱስ ዮሐንስ ዘኢየሩሳሌም እኛስ ኃጢአታችንን ለማስተሥረይ በሥጋ እንደታመመ፤ እንደሞተ፤ ከነፍሱም በተለየ ጊዜ ሥጋውን እንደገነዙ፤ ከሙታንም ተለይቶ በእውነት እንደተነሣ፤ ከተነሣም በኋላ በእውነት ወደ ሰማይም እንደ ዐረገ እናምናለን፡፡ ኋላም እርሱ በሚመጣው ዓለም በሕያዋን በሙታን ይፈርድ ዘንድ ይመጣል፤ የሰውን ወገኖች ሁሉ በሞቱበት፤ በተቀበሩበት ሥጋ ከሞት ያስነሣቸዋል፤ ከትንሣኤውም በኋላ ያለመለወጥ ሁል ጊዜ ይኖራል፤ እርሱ በዚህ በሞተበት፤ በተገነዘበት ሥጋ ከሙታን አስቀድሞ እንደተነሣ፡፡/ቅዱስ ዮሐንስ ዘኢየሩሳሌም ሃይ. አበ. 52፥11-12/ በማለት ክርስቶስ ስለእኛ ኃጢያት እንደሞተና እንደተነሳ አስተምሯል፡፡ የሥጋን ሕማም ለመለኮት ገንዘብ በአደረገ ጊዜ የእግዚአብሔር አካል በባሕርዩ በግድ ሕማምን አልተቀበለም፤ ሕማም በሚስማማው ባሕርዩኃይልን እንጂ፤ ሞትም በሥጋ ለእግዚአብሔር ቃል ገንዘብ በሆነ ጊዜ ሞትን አጠፋ፤ ከሞትም በኋላ ፈርሶ በስብሶ መቅረትን አጠፋ፡፡/ቅዱስ ቴዎዶጦስ ሃይ. አበ. 53፥27/ ሲል መለኮት ሥጋን ተዋሕዶ ማዳኑን ተናግረዋል፡፡ ክርስቶስ የሙታን በኲር እንደምንተባለ? እነሆ በናይን ያለች የደሀይቱን ልጅ አስቀድሞ አስነሣው፤ ዳግመኛም አልዐዛርን በሞተ በዐራተኛው ቀን አስነሣው፡፡ ኤልያስም አንድ ምውት አስነሣ፤ ደቀ መዝሙሩ ኤልሣዕም ሁለት ሙታን አስነሣ፤ አንዱን ሳይቀበር፤ ሁለተኛውን ከተቀበረ በኋላ ሥጋውን አስነሣ፡፡ እነዚያ ሙታን ቢነሡ ኋላ እንደ ሞቱ፤ እነርሱ ኋላ አንድ ሆነው የሚነሡበትን ትንሣኤ ዛሬ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የሙታን ትንሣኤያቸው በኲር ነው፤ እንግዲህ ወዲህም ሞት የሌለበትን ትንሣኤ አስቀድሞ የተነሣ እርሱ ነው፤ ዳግመኛም ሞት አያገኘውም ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ /ቅዱስ ኤጲፋንዮስ. 57፥3-6/ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ ስለክርስቶስ ሥጋና ነፍሱ ሲናገር ቃል ሥጋውን በመቃብር አልተወም፤ በሲኦልም ካለች ከነፍሱ አልተለየም፤ ከነፍስ ከሥጋ በአንድነት ነበረ እንጂ፤ ለዘለዓለም ክብር ምስጋና ይግባው፡፡ /ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ ሃይ. አበ. 60፥29/ ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ በትንሣኤ ከእናንተ ጋር እስከምመጣበት ቀን ድረስ ከዚያ ወይን ጭማቂ አልጠጣም፤ በሐዲስ ግብር በምነሣበት ጊዜ የምታዩኝ እናንት ምስክሮቼ ናችሁ ያለውን የማቴዎስን ወንጌል በተረጎመበት አንቀጽ እንዲህ አለ፡፡ ሐዲስ ያለው ይህ ነገር ምንድነው? ይህ ነገር ድንቅ ነው! መዋቲ ሥጋ እንዳለኝ ታያላችሁ፤ ነገር ግን ከትንሣኤ በኋላ የማይሞትነው፤ አይለወጥም፤ ሥጋዊ መብልንም መሻት የለበትም፤ ከትንሣኤ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ቢበላም ቢጠጣም መብልን ሽቶ አይደለም፤ እርሱ ከሙታን ተለይቶ እንደተነሣ ያምኑ ዘንድ በላ ጠጣ እንጂ፡፡ ይህ ድንቅ ሥራ ነው! ያለ መለወጥ ሰው የሆነ ቃል የተቸነከረበትን ምልክት /እትራት/ አላጠፋምና፡፡ በሚሞቱ ሰዎች እጅ እንዲዳሰስ አድርጎታልና፤ አምላክ የሆነ ሥጋ የሚታይበት ጊዜ ነውና አላስፈራም፤ እርሱ በዝግ ደጅ ገባ፤ ግዙፉ ረቂቅ እንደሆነ ሥራውን አስረዳ፤ ነገር ግን በትንሣኤው ያምኑ ዘንድ የተሰቀለው እርሱ እንደሆነ የተነሣውም ሌላ እንዳይደለ ያውቁ ዘንድ ይህን ሠራ፡፡ ስለዚህም ተነሣ፤ በሥጋውም የችንካሩን ምልክት /እትራት/ አላጠፋም፤ ዳግመኛም ከትንሣኤው አስቀድሞ ደቀ መዛሙርቱ ጧት ማታ ከእርሱ ጋር ይበሉ እንደነበረ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በላ፤ ስለዚህም በዐራቱ መዓዝነ ዓለም ትንሣኤውን አስረዱ፤ ከትንሣኤውም በኋላ ያየነው ከእርሱም ጋር የበላን የጠጣንም እርሱ ነው ብለው አስረዱ፡፡በማለት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አስረድቷል፡፡ /ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሃይ. አበ. 66፥7-12/ ቅዱስ ቄርሎስ በትንሣኤው ያገኘንውን ክብር ሲገልጽ በእርሱ ሞት ከብረናል፤ በመለኮቱ ሞት ሳይኖርበት በሥጋ ሞተ፤ ምንጊዜም ቢሆን እርሱ የሕይወት ልጅ ሕይወት ነው፤ ይኸውም ከእግዚአብሔር አብ የተወለደው ልደት ነው፡፡ ክርስቶስ በሥጋ በመጣ ጊዜ ሞት እንዲህ ድል ተነሣ፤ መፍረስ መበስበስም በእርሱ /በክርስቶስ/ እንዲህ ጠፋ፤ ሞትም ድል ተነሣ፡፡ ሕማምን ሞትን ገንዘብ አደረገ፤በሥጋው የሞተው ሞትም የእኛን ባሕ ርይ በመዋሐዱ ነው፤ ከዚህ በኋላ ተዋሕዶውን አስረዳ፤ ሞት ሰው የመሆን ሥራ ነውና፤ ከሙታን ተለይቶ መነሣትም አምላክ የመሆን ሥራ ነውና፤ እነዚህ ሁለት ሥራዎችን /ሞትን፤ ትንሣኤን/ እናውቃለን፡፡ በሥጋ ሞተ እንዳልን ዳግመኛ በሥጋ ተነሣ እንላለን፤ ስለ ትንሣኤም የእርሱ ገንዘብ እንደሆነ፤ ሙስና መቃብርም እንዳላገኘው ይነገራል፤ ይህ ለመለኮት አይነገርም፤ የተነሣው ሥጋው ነው እንጂ፡፡/ቅዱስ ቄርሎስ ሃይ. አበ. 72፥12፣72፥35፣ 79፥9/ የሞትን ሥልጣን አጠፋ፤ ዲያብሎስንና ኃይሉን /ኃጢአትን/ ሻረ፤ የብረት መዝጊያዎችን ሰበረ /ፍዳ መርገምን አጠፋ/፤ ሲኦልን በዘበዘ፤ የጣዖት ቤቶችን አፈረሰ፤ የምሕረትን በር ከፈተ፤ ይህችውም በደሙ የከበረች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ለሁሉ የዘለዓለም ሕይወት መገኛ የሚሆን ልጅነት የተገኘበት ሥጋውን ደሙን ሰጠን፡፡ /ቅዱስ ቴዎዶስዮስ ሃይ. አበ. 83፥6/ ሲል ቅዱስ ሳዊሮስ ደግሞ ለእኛስ እግዚአብሔር ቃል በባሕርየ መለኮቱ እንደታመመ፤ እንደሞተ፤እንደተቀበረ ልንናገር አይገባንም፡፡ ከሙታን ተለይቶ በመነሣቱ ሞት የሌለበት እንደሆነ፣ መድኀኒታችን በሚሆን በሞቱና በሦስተኛው ቀንም በመነሣቱ ትንሣኤን እንደሰጠን እናምናለን፤ የሞተ እርሱ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷልና፡፡ ሁሉን የሚችል እርሱ ካልተነሣ፣ የችሎታ ሁሉ ባለቤት እርሱ የሌለ ከሆነ፣ እንኪያስ ትንሣኤም ሐሰት ነዋ! ትንሣኤም ሐሰት ከሆነ ሃይማኖታችን ከንቱ ነው፤ እንኪያስ አይሁድንም እንመስላቸዋለን፡፡ ሰው እንደመሆኑ በሥጋ ባይሞትስ በሞት ላይ ሥልጣን ያለው አምላክ እንደመሆኑ ሞትን ባላጠፋ ነበር፡፡ የአዳም የዕዳ ደብዳቤም ከእግዚአብሔርና ከሰው መካከል ባልተደመሰሰም ነበር፡፡/ቅዱስ ሳዊሮስ ሃይ. አበ. 84፥18-20/ በማለት ሞት በክርስቶስ ሞት መደምሰሱን አስረድተዋል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ዘአንጾኪያና ቅዱስ ቴዎዶስዮስ ፈጣሪያችን ክርስቶስ ለጌትነቱ እንደሚገባ ሥጋ መለወጥ የሌለበት እስኪሆን ድረስ ድንቅ በሚያሰኝ ትንሣኤ ሙስና መቃብርን አጥፍቷልና፤ በሥጋ በተቀበላቸው በሚያድኑ በእነዚህ ሕማማት ከጽኑ ሞት፣ ከዲያብሎስም ሥልጣን ያድነን ዘንድ ወደ ቀደመ ቦታችንም ያገባን ዘንድ፡፡ ይታመም ዘንድ በተገባው በሥጋው፣ ነውር የሌለበትን ሕማም በፈቃዱ በእውነት ተቀበለ እንጂ፤ በምትሐት እንዳልታመመ እናገራለሁ፤ እንደሕማሙ ሞትንም በመስቀል ላይ ተቀበለ፡፡ ለአምላክነቱ በሚገባ፤ ድንቅ በሚያሰኝ ትንሣኤውም የጌትነቱን ሥልጣንገለጠ፡፡ ሥጋውንም የማይሞት አደረገ፤ ከኃጢአት በራቀ በንጹሕ ማኅፀን በተዋሐደው ጊዜ ለመለኮት ገንዘብ ስለሆነበሥራው ሁሉ አይለወጥም፡፡በማለት የሰው ልጅ በክርስቶስ ሞት ወደ ቀደመ ርስቱ መመለሱን ጽፈዋል፡፡ /ቅዱስ ዮሐንስ ዘአንጾኪያ ሃይ. አበ. 90፥34፣ቅዱስ ቴዎዶስዮስ ሃይ. አበ. 92፥15/ ሕማም የማይስማማው እርሱ በሥጋ ሞትን ታገሠ፤ ብረት ወደ እሳት በገባ ጊዜ ሁለንተናው እሳት እንደሆነ እስኪታሰብ ድረስ በእሳት ዋዕይ እንዲግል፣ በመዶሻ በተመታ ጊዜ በመስፍሕ /መቀጥቀጫ/ ላይ እንዲሳብ /እንዲቀጠቀጥ/፤ እሳትም ከብረት ጋር ተዋሕዶ ሳለ ፈጽሞ እርሱ እንዳይመታ፤ ከብረቱም እንዳይለይ፣ ግን የመዶሻ ኃይል ሳያገኘው እንዲመታ፤ ለመዶሻ እንዲሰጥ፤ የሚያድን የጌታ ሕማም እንዲህ እንደሆነ ዕወቅ፡፡ በዚህ ትንሽ ምሳሌ፤ በእሳትና በብረት ተዋሕዶ ምልክትነት ፍጹም ተዋሕዶን እንወቅ፤ የእግዚአብሔር ቃል ይህ መከራና ሕማምን የሚቀበል ሥጋን ተዋሕዶ በሞተ ጊዜም ከሦስት ቀን በኋላ አምላክነቱ በተገለጠበት ትንሣኤው ሞትን አጠፋው፤ ሥጋው በመቃብር በመቀበሩም በመቃብር ውስጥ የነበረ መፍረስን መበስበስን አጠፋልን፤ ከሥሩም ነቀለው፤ ይህንም የሚያስረዳ ከቅዱሳን ወገን ብዙ ሰዎች ተነሡ፡፡/ቅዱስ ባስልዮስ ሃይ. አበ. 96፥50-52/ ቅዱስ ዲዮናስዮስም ዳግመኛ እርሱ እንደሞተ በሦስተኛውም ቀን እንደተነሣ፣ ስለተነሣም ሥጋው የማይፈርስ የማይበሰብስ፣ የማይታመም፣ የማይሞት እንደሆነ እናምናለን፡፡ ሥጋውም ከእርሱ ጋር አንድ ሆኖ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአርያም በልዑል ዙፋኑ ተቀመጠ፤ ዳግመኛም በሙታንና በሕያዋን ይፈርድ ዘንድ ሁሉ አንድ ሆኖ በሚነሣበት ጊዜ እርሱ በጌትነት ይመጣል፤ ለሁሉም እንደሥራው ይከፍለዋል፤ እኛ በእነዚህ ቃላት ሳናወላውል ጸንተን እንኖራለን፡፡ /ቅዱስ ዲዮናስዮስ ሃይ. አበ. 99፥32/ እንዲሁም ቅዱስ ፊላታዎስ በፈቃዱ በሥጋው የእኛን ሕማም ታመመ፤ በእውነት የእኛን ሞት ሞተ፤ ይኸውም የነፍስ ከሥጋ መለየት ነው፤ በፈቃዱ በተለየ አካሉ ሞትን ገንዘብ አደረገ፡፡ በሦስተኛውም ቀን በሥልጣኑ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአባቱ ዕሪና ተቀመጠ፤ በኋለኛይቱ ቀንም በሙታን በሕያዋን ሊፈርድ ይመጣል፡፡ /ቅዱስ ፊላታዎስ ሃይ. አበ. 105፥14/ በማለት ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ እንዳረገ ጽፈዋል፡፡ ቅዱስ ዲዮናስዮስ ስለሞት መደምሰስ ሲናገር በሞቱ ሞትን ያጠፋው እሱ ነው፤ በሦስተኛው ቀን በመነሣቱም ሲኦልን በዘበዘ፣ ለሁሉም ትንሣኤን ገለጠ፡፡ ፈጽሞ አልተለወጠም፤ ለሁሉ አምላክነቱን አስረዳ፤ ሙስና መቃብርን ከእኛ አጠፋ፤ በቀደመ ሰው በአባታችን በአዳም ትእዛዝ ማፍረስ ምክንያት ሠልጥኖብን ለነበረ ኃጢአት ከመገዛት አዳነን፡፡ብሏል፡፡ /ቅዱስ ዲዮናስዮስ 111፥13/፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ሲል በፈቃዱ ሞቶ እንደተነሳ ሲናገር እሑድ በመንፈቀ ሌሊት ነፍሱን ከሥጋው አዋሕዶ በመለኮታዊ ኃይል ተነሣ፤ እርሱ ራሱ ነፍሴን በፈቃዴ አሳልፌ ልሰጥ ሁለተኛም መልሼ ላዋሕዳት ሥልጣን አለኝ እንዳለ፡፡ በነጋም ጊዜ ለማርያም መግደላዊት ታያት፤ እጅ ልትነሣው በወደደች ጊዜም አትንኪኝ አላት፤ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና፤ ስለዚህም ሥጋዊ አካሉ ከዚያን አስቀድሞ በአብ ቀኝ እንዳልተቀመጠ ዐወቅን፡፡ በተነሣም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ነገር እንደተናገረ አሰቡ፡፡ በመጽሐፍና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም የተናገራቸውን ቃል አመኑ፤ ሁለተኛም ነፍሴን በፈቃዴ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ ልለያት መልሼም አዋህጄ ላስነሣት ሥልጣን አለኝ፡፡ ዳዊትም አቤቱ የመቅደስህን ታቦት ይዘህ ተነሥ ይላል፡፡ ነቢዩ አቤቱ አንተ የመቅደስህን ታቦት ይዘህ ተነሥ ለምን አለ? የመቅደሱ ታቦት ከሆነችው ከዳዊት ዘር ከነሣው ሥጋ ጋር በመለኮታዊ ኃይሉ ከሞት እንቅልፍ ከመንቃት በስተቀር የእግዚአብሔር መነሣት ምንድነው?/አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈ ምሥጢር ዘትንሣኤ 77-79፣95/ ብሏል፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በቅዳሴው ስኢየሱስ ክርስቶስ ሞት፣መቃብርና ትንሣኤ ሲናገር ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከጲላጦስ ተካስሰው ከመስቀል አውርደው፣ በድርብ በፍታ ገንዘው በአዲስ መቃብር ቀበሩት፡፡ በሦስተኛው ቀን መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት በዝግ ቤት ገብቶ በጽርሐ ጽዮን ታያቸው፡፡ ብሏል፡፡ /ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ 1፥29-31/ በሠለስቱ ምዕትና በያዕቆብ ዘስሩግ ቅዳሴ ክርስቶስ ስለሰው ፍቅር መሞቱና መነሳቱ ተገልጿል፡፡ ሰውን ስለመውደድህ ይህን ሁሉ አደረግህ፤ ከሙታን ተለይተህ መቃብር ክፈቱልኝ፤ መግነዝ ፍቱልኝ ሳትል ተነሣህ፡፡ ከእግረ መስቀል ሙታንን አስነሣህ ነፍሳትን ከሲኦል ማርከህ ለአባትህ አቀረብህ፡፡ በታወቀች በተረዳች በሦስተኛይቱ ቀን መቃብር ክፈቱልኝ፤ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ተነሣ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት በዝግ ቤት ገባ፤ የተወጋውን ጎኑን፤ የተቸነከረውን እጁን፣ እግሩን አሳያቸው፡፡ በዓለመ ነፍስ የሆነውን እያስተማራቸው ዐርባ ቀን ኖረ፡፡ /ቅዳሴ ያዕቆብ ዘስሩግ 1፥24፣ቅዳሴ ዘሠለስቱ ምዕት 4፥25-27/ ሰማያት /ሰማያውያን መላእክት /የደስታ በዓልን ያደርጋሉ፤ ደመናት /ቅዱሳን/ የደስታን በዓል ያደርጋሉ፣ ምድር /ምድራውያን ሰዎችም/ በክርስቶስ ደም ታጥባ /ታጥበው/ የፋሲካን በዓል ታደርጋለች /ያደርጋሉ/ ያከብራሉ /ታከብራለች/፡፡ ዛሬ በሰማያት /በሰማያውያን መላእክት/ ዘንድ ታላቅ ደስታ ሆነ፤ ምድርም በክርስቶስ ደም ታጥባ የፋሲካን የነጻነት በዓል ታደርጋለች፡፡ የትንሣኤያችን በኲር ክርስቶስ ከሙታን ሁሉ ተለይቶ ቀድሞ ተነሣ፡፡ /ድጓ ዘፋሲካ/ |